መለኪያውን የማያውቅ ልኩን አያውቅም – በመርዓዊሥላሴ ንጉሤ

መለኪያውን የማያውቅ ልኩን አያውቅም  – በመርዓዊሥላሴ ንጉሤ

የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና ማቴ 5:5

እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል 25

 

www.Tsega.com: ይህን ጽሁፍ ለመረዳት በቅድሚያ ብፁዓን የሚለውን ቃልና “የተራራው ትምህርት” በመባል የሚታወቀውን በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ ምዕራፍ 7 የሚገኘውን የጌታ እየሱስ ትምህርት መዳሰስ ወይም በትንሹ መረዳት ያስፈልጋል:: ብዙዎች “ይሄ “የተራራው ትምህርት” የሚቻል አይደለም” በማለት ሲሸሹት አንዳንድ አማኞች ደግሞ ይህን የተራራው ትምህርት “የተፈራው ትምህርት” እያሉ ይጠሩታል። ይህም አገላለጥ ትምህርቱ በአማኞች እንኩዋን ምን ያህል የተፈራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው:: ይህ የተራራው ስብከት ግን ጌታ እየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ተራራ ወስዶ የነገራቸው ትእዛዛትና መመርያዎች የታጨቁበት የአዲስ ኪዳን ትምህርት ነው። ትምህርቱ ሲጀምርም ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ(ማቴ5:1) በማለት ስለሚጀምር፣ ከዚህ በመነሳት “የተራራው ትምህርት ወይም ስብከት” በመባል ይታወቃል::

ይህን ክፍል ማስተማር ብቻ ሳይሆን እራሱ ጌታ እየሱስ በምድር ሲመላለስ ያስተማራቸውን ትዕዛዛቱን ሁሉ በህይወቱ በተግባር አሳይቶናል:: ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ተራራ ወስዶ ይህን ትምህርት ያስተማረበት ዋና ምክንያት የጌታ ተከታይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በዚህ እግዚአብሔር በወሰነው የኑሮና የህይወት ልክ እንዲገለጡ የሚያደርግ ተግባራዊ መመርያ በዝርዝር የሚገኝበት በመሆኑ ነው:: የኑሮና የህይወት ልክ አለ ማለት ነው ወይም ልኬን ልትነግረኝ ትችላለህ ማለት ነው። ልክ ልካችንን ሊነግረን የሚችል መለኪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ በማለት በ650 ገጽ መጽሓፉ የሚሞግተው ወንድም መርዓዊስላሴ ከአዲስ አበባ ነው:: በቅርቡ ወንድማችን መጋቢ መርዓዊስላሴ ይህንን የተፈራውን የተራራውን ስብከት የክርስትያኖችን የህይወት ጥራትና ደረጃ የሚጠቁም ከሰማይ የተለቀቀ ቱንቢ ነው በማለት ቱንቢ በተባለው መጽሐፉ በሚያስደንቅ አገላለጽ ተንትኖታል::

ጸሐፊው የተራራው ስብከት ላይ የሚገኙት ትምህርቶች አይቻሉም ተብለው የሚሸሹ ሳይሆን ትምህርቱ ለክርስትያኖች የህይወት መለኪያ ቱንቢ ነው፡ ልክ እግዚአብሔር ”እነሆ በህዝቤ በእስራኤል መሃከል ቱንቢ አደርጋለሁ (አሞ 7:7_8) እንዳለን ሁሉ ይለናል:: ቱንቢ ግንበኞች የሰሩት ግንብ ወይም ያቆሙት ምሶሶ ቀጥ ማለቱን ወይም መጣመሙን የሚለኩበት መሳርያ ነው:: ግንበኛ ከመሰረቱ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሚሰራውን ግንብ በቱንቢ በመለካት ያረጋግጣል። ልክ እንደዚሁ የተራራው ትምህርት ውስጥ ያሉት ጠንካራ ትዕዛዛትም እያንዳንዱ ክርስትያን ከመሰረቱ ጀምሮ ኑሮውና ህይወቱ እንዴት እያደገ እንደሆነ የሚለካበትና የሚመዝንበት ጠቃሚ መለኪያ ነው::

ብዙዎቻችን በዚህ በ”ተራራው ስብከት” ውስጥ የምናየውን ፍጹም ትምህርት እንፈልጋለን ለመሆንና ለማድረግም እንጥራለን:: መፈለጋችን መልካም ጅማሬ ሲሆን ለመሆንና ለማድረግ ግን በጌታ ጸጋ መደገፍ እንደሚያስፈልግ እንዳትረሱ:: እየሱስ ትዕዛዛቱን ብቻ ሳይሆን ትዕዛዙን ልንፈጽም የምንችልበትን ጉልበት እንደሰጠን ማስታወስም ያሻል። ጸጋው የተሰጠን በላቀ ማንነት እንድንገለጥ የሚያስችል እንደሆነ መዘንጋት ግን አይገባም።( ቲቶ 2: 11 ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ ። ) ልብ በሉ ይህቺ እንደገና ተወልደን የምንገባባት የእግዚአብሔር መንግስት የምትተዳደረው በሌላ ሕግ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ቃል ነው። የመንግስቱን ዜግነት ያገኘን ነዋሪዎች የሆንን ደግሞ አኗኗራችን የእግዚአብሔርን መንግስት በሚወክል ህይወት የሚገለጥ መሆን አለበት።

ዛሬ በአንድ በር በችኮላ እየገባ ደቀ መዝሙር ሳይሆን በሌላ በር ሳይበስል ለሚወጣው የዘመኑ ክርስትያን የተራራው ስብከትን የመሰለ ቱንቢ መኖር ከመቼውም በላይ አስፈላጊ ነው:: የቱንቢም ጸሐፊ “የዘመናችን ክርስትና ዋነኛ ችግር ብዙ መሳታችን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ስተን ስንጣመም አለማወቃችንም ጭምር ነው ይለናል ። ጽሁፉን ያቀረብነው ልንለካችሁ ሳይሆን እራሳችንን የምንለካበት ቱንቢ መኖሩን ለመጠቆም እና ህይወታችንን መርምረን ወደ ልካችን እንድንደርስ ለማበረታታ ነው:: ለዛሬው ከዚሁ ከተራራው ትምህርት ውስጥ አንቀጸ ብፁዓን (the Beatitudes ) ተብለው ከሚጠቀሱት ስምንቱ ብፁዓኖች አንዱን ፦ የዋህነትን እንደ ቱንቢ ይዘንላችሁ ቀርበናል። ቃሉም እንዲህ ይላል ፦የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና (ማቴ 5:5)።

የብፅዕና ትምህርት፣ ከምድር የደስታ ምንጭና መለኪያ ጋር የሚቃረኑ አስተሳሰቦች የሞሉበት በመሆኑ፣ ዓለም ልትቀበለው ቀርቶ ልትሰማው እንኳ ፈቃደኛ አይደለችም። እናንተም ብትሆኑ አስተሳሰቦቹ በሌሎች ዘንድ ለምን ተቀባይነት አላገኙም? ብላችሁ እራሳችሁን ማድከም አይጠበቅባችሁም። አስተውሉ! እነዚህን የብፅዕና እውነቶች በየእለቱ ስትኖሯቸው፣ የክርስቶስ መዓዛና ሽታ ለሌላው ሰው ማወድ ይጀምራል። የቀደሙት ቅዱሳን፣ ዓለምን መቀየር የቻሉበትን ምስጢርም ስታጠና ከጀርባቸው ታላቁ የብፅዕና እውነት በአንድም ወይም በሌላ መንገድ ተገልጦባቸው እንደነበር ትገነዘባለህ። ዳሩ ግን መቼም ጊዜ ቢሆን የራስህን ፈቃድ፣ የስጋህን ምኞትና ፍላጎት እየፈጸምክ የብፅዕናን ህይወት እኖራለሁ ብለህ በጭራሽ እንዳታስብ።

ብፁዓን የሚለውን የአማርኛ ቃል በተለምዶ እንደ ሹመት ሲለጠፍ ስለሆነ የሰማነው ብዙዎቻችን በተለየ የመንፈሳዊነት ብቃት ጣራ ላይ ላሉ ሰዎች የሚሰጥ አድርገን እናየው ይሆናል። በጌታ እየሱስ የተራራው ትምህርት ላይ ያለው ብፅዕና ግን “በመለኮታዊ ባርኮት የሆነ ጥልቅ ደስታ “ የሚል ትርጉም አለው። የእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስም ብፁዓን የሚለውን ቃል ብሩካን ( BLESSED ) ይለዋል:: ስንቶቻችን ነን እባክህ እገሌን ወይም እገሊትን ባርካት ስንል እንደ እነዚህ ስምንት ብፁዓን እንዲሆኑ የምንጸልየው? እከሌን የዋህ፣ስለ ጽድቅ የሚሰደድ ፣የሚያዝን፣ በመንፈስ ድሀ አድርገው፣ እያልን የምንጸልየው?

ደስታን ፍለጋ ሰዎች በራሳቸው መንገድ በሚባዝኑበት ባለንበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን በጌታ እየሱስ ላመኑ ሁሉ ጥልቅ የሆነ፣ከሰማይ የሚወጣ፣የማይረበሽና፣የማይታወክ ውስጣዊ ደስታ፣ሃሴትና ፍሥሐ ወይም ብፅዕና እንድንልማመደው ተሰጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስም “በጌታ ደስ ይበላችሁ” ሲለን ይህን እውነተኛ ደስታ ከእውነተኛው ምንጭ በመቅዳት እንድንለማመደው ሲያሳስበን ነው። ሆኖም ግን ልብ በሉ፣ አማኞች ዓለምን እስካልናቁ ድረስ፣በኢየሱስ የተገለጠው የደስታ ልክ ላይ ደርሰው ሊያጣጥሙት አይችሉም። እስቲ ለዛሬ ከስምንቱ ብፁዓን አንዱን/የዋህነትን እንደ ቱንቢ ተጠቅመን ራሳችንን እንመርምር::

አዲስ ኪዳን መጀመርያ የተጻፈበት የግሪኩ ቋንቋ “ የዋህነት” የሚለውን ቃል ሲተረትረው ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ‘ረጋ ያለ ወይም ’ ወይም ‘እርጋታ’ ያለው ባህሪ ማሳየት ማለት ነው ይለዋል:: ጌታ እየሱስም “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” (ማቴ 5:5) ሲል በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ስፍራ ያሳየናል:: የዋህነት ሌላውን ለመርዳት በትህትና ጎንበስ ማለት ይጠይቃል:: ጌታ እየሱስም የራሱን ባህሪውን ሲገልጽ “ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፡ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ “ ብሎናል (ማቴ 11:29)። ይህን ሃሳብ የተረዳውም ጳውሎስ “በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ”(2 ቆሮ 10:1) ሲላቸው በየዋህነቱ የተረጋገጠለትን ክርስቶስን ምሰሉ ማለቱ ነበር። ዶ/ርመለሰ ወጉ “ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች” በሚለው መጽሐፋቸው “የዋህነት ከስጋ ልብ የሚመነጭ የተፈጥሮ ባህሪ ወይም የስነ አእምሮ ጥበብ የፈጠረው አይደለም:: ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በአረሰረሰው ልብ ውስጥ የሚበቅል ፍሬ ነው” በማለት ይገልጹታል። አያይዘውም “የዋህነት እግዚአብሔር በሰጠን ኀይል ተጠቅመን፣የራሳችንን ስሜትና ድርጊት ተቆጣጥረን፣እንደ እኛ ድካምና ፍላጎት ሳይሆን፣እንደ ፍላጎታቸው ሌሎችን ለማስተናገድ የሚያስችል በቁጥጥር ውስጥ የዋለ ኅይል ነው” ይላሉ::

እኛ በምንኖርበት ህብረተሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ኅይልን፣ ስልጣንን፣ እንዲሁም ከሌላው መቅደምን በኅይል የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ የዋህነትን ዝቅተኛ ባህሪ እንደ ሆነ አድርገው ይመለከቱታል:: ሰው እርስ በርሱ በሚበላላበት፣ አምባገነንነትና ኅይለኛነት ባየለበት በአሁኑ ዘመን፣ የዋህነት በብዙዎች ዘንድ የሚፈለግ ባሕሪ አይደለም። ምክንያቱም የዋህነት በአሁኑ ዘመን፣ በብዙዎች ዘንድ ትርጉሙ “ሃሞት የለሽነት”፣ አቅመቢስነት፣ ደካማነትና ፈሪነት” መስሎ ስለሚታይ ነው። ብዙዎች “ኅይለኛ” በመሆን፣ ታግሎ በማሸነፍ ወይም ሌላውን ጠልፎ በመጣል ነው የሚሳካልን የሚል የተሳሳተ እምነት ስላላቸው፣ “የዋህ በመሆን ራሳችንን ወደ ኋላ ማስቀረት የለብንም” ይላሉ። ክርስትያኖችስ ስለ የዋህነት ያላቸው አመለካከት ከዓለማውያን ይለይ ይሆን? ስለ ብዙ ነገሮች ጌታ እንዲያበዛልን ጸልየናል። የየዋህነትን መንፈስ እንዲያበዛልን ግን ስንቶቻችን ጸልየን ይሆን? ይሄ የየዋህነት ፍሬ መታየት ያለበት በታላላቅ መንፈሳዊ ሰዎች ህይወት ውስጥ ብቻ ነው ብለን እንገምት ይሆን?

እስቲ የዋህነትን የሚያሳዩ ትረካዎችን እናሰማችሁ። የመጀመርያው በመጋቢ መርዓዊ ከተጻፈው ቱንቢ የተወሰደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ” ከሚለው ከመጋቢ ዶ/ር መለሰ ወጉ መጽሐፍ ፣ ሶስተኛው ደግሞ ከመጋቢ ዶ/ር ተስፋ ወርቅነህ “ የክርስትና እድገት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ ነው::

ክርስትያኖች በእምነታቸው ምክንያት በልዩ ልዩ መከራ በሚያልፉበት ዘመን፣ጌታን ከልቡ የሚወድ አንድ አማኝ በአደገኛ ወህኒ ተጣለ። እንደ አጋጣሚ እርሱ በታሰረበት ጠባብ ክፍል ውስጥ አንድ ጨካኝ ወንጀለኛ ቀድሞ ታስሮ ኖሮ፣ ከገባ ጀምሮ እየተነኮሰ ምቾት እንዳይሰማው ይፈታተነው ጀመር። ይባስ ብሎ በቀን አንዴ የምትሰጣቸውን ትንሽ ቁራሽ ዳቦ ከእጁ ቀምቶ በላበት። ክርስትያኑ ግን ክፉ ነገር ሳይናገር ውሃውን ብቻ ጠጥቶ አደረ። በነጋ ጊዜም ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ በጥሩ ሰላምታ አናገረው፡ እርሱ ግን በሁለተኛውም ቀን ዳቦውን ወስዶ በላበት።በዚያም ቀን አንዳችም ክፉ ቃል ከአፉ ሳይወጣው፣ሳይቆጣና ሳይማረር ውሃውን ግጥም አድርጎ ከጠጣ በኋላ አመስግኖ ተኛ። በሶስተኛው ቀን የቀረበላቸውን ዳቦና ውሃ ተቀብሎ፣ እንደ ልማዱ ጸልዮ ቀና ሲል ዳቦው ከፊቱ ተቀምጦ አገኘው፡ እርሱግን” ይህንንም ጨምረህ ብትበላ እኮ ደስ ይለኛል” ሲል የእስር ቤት ወዳጁን ከልቡ ጋበዘው። ዕድሜውን በሙሉ ለሰዎች ቀና አመለካከትና ደግነት ኖሮት የማያውቀው ያ ሰው፣ ግን በተደረገለት ቸርነት ከማመስገን ይልቅ እጅግ ተጠራጥሮ “ባለፉት ሦስት ቀናት ምንም ነገር አልቀመስክም፣ታድያ የዛሬም ድርሻህን ልትሰጠኝ የፈቀድከው ከእኔ ምንፈልገህ ነው? ሲል ዓይኖቹን እያጉረጠረጠ ጠየቀው።

አማኙም ሰው ረጋ ብሎ “አየህ ወዳጄ፣የእኔና የአንተ ጓደኝነት ከተጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀናችን ነው፡ በእነዚህ ቀናት እንደ ተመለከትኩት ከሆነ ታድያ ፣ አንተ ብትሞት የምትሄድበትን የምታውቅ አልመሰለኝም፡እኔ ግን አሁን ብሞት የት እንደምሄድ አውቃለሁ፡ ስለዚህ ከእኔ ይልቅ አንተ በህይወት መኖርህ አስፈላጊ እንደ ሆነ ስላሰብኩ ድርሻዬን ወስደህ ስትበላ ደስተኛ ነበርኩ“ አለው። ምን ማለቱ እንደሆነ እንዲያብራራለት ሲጠይቀው ስለ ሞትና ትንሣኤ፣ስለ ዘላለም ሕይወትና ፍርድ እንዲሁም ስለ ጌታ እየሱስ በዝርዝር አስረዳው። ሰውየው በነገሩ ተመስጦ ሲያበቃ “ለመሆኑ ይህ እየሱስ ያልከው ማንን ይመስላል?“ ሲል ያልጠበቀውን ጥያቄ ጠየቀው። እርሱም አፉ ላይ ድንገት እንደ መጣለት “ችግር የለም ፣ ነገ አሳይሃለሁ” ሲል ቃል ገባለት።

ነገሩን ሲያስበው ግን “ነገ አሳይሃለሁ” ብሎ በድፍረት በመናገሩ ተጸጸተ፡ በዚያች ጠባብ እስር ቤት ጌታ ወርዶ ለዚያ ሰው እንዲታይለትም ከልቡ ይጸልይ ጀመር፡ እኩለ ሌሊት ሲሆን፣ የጌታ ድምጽ በራዕይ ወደ እርሱ ደርሶ “እኔ አልመጣም፡ አንተ ግን እኔን ይመስላል ብለህ ንገረው” ሲለው ደግሞ ፣ይበልጥ ተጨነቀ፡ “ጌታ ሆይ ፣ እኔን ይመስላል እንዴት እለዋለሁ? እኔ እኮ ፣ አንድ ምስኪን እስረኛ ነኝ” በማለት ለሰከንድ እንኳ ታይቶለት ይመለስ ዘንድ ቢማጠነውም አንዳች የተለየ ነገር ሳይሆን ጎህ ቀደደ። ጠዋት ሰውየው ቀድሞ ተነሥቶ “የነገርከኝ ኢየሱስ ማንን እንደሚመስል አሁን ትነግረኛለህ?“ አለው ኮስተር ብሎ ፡ እርሱም “አዎን” አለ ሲፈራ ሲቸር “እኮ ፣ማንን ይመስላል?” አለው፣ ዓይኖቹን ከእርሱ ሳይነቅል፣ ፍርጥም ብሎ ፡አማራጭ ያጣው ያም ሰው እየተሳቀቀ፡ “እኔን ይመስላል አለው”፣ በዚያን ጊዜ ያ ወንጀለኛ ሰው ድንገት በጉልበቱ ተንበርክኮ “የምር አንተን የሚመስል ከሆነስ ለዘላለም ይግዛኝ” ብሎ ራሱን ለእየሱስ ክርስቶስ አሳልፎ ሰጠ።

የመንፈሳዊ ሕይወት እድገት ግቡ ክርስቶስን መምሰል ነው። ክርስቶስን መምሰል የምንችለውም በባህርይ ነው። የዋህነት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱና በምድር ጌታ እየሱስን ከሚያስመስሉን ባህርያት አንዱ ነው። የዋህነትና ሌሎችም ከመንፈስ ፍሬዎች የሚመጡ ባህርያት በህይወታችን እየበዙና እየበለጸጉ በሚሄዱበት ጊዜ የክርስቶስን መልክ እየወረስን እንሄዳለን።

ጌታ እየሱስ ይህን ብልጣ ብልጥ፣ የሸፍጥ ዓለም በደንብ አድርጎ ያውቀዋል። ለደቀ መዛሙርቱ “እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ (ማቴ 10:16) ማለቱ ግን የዋህነትን የሚከተል ሌላ ልባምነት የሚባልና ከአደጋ የሚጠብቀን መኖሩን ያሳየናል። እየሱስ እንደ እርግብ የዋህ፣ እንደ እባብም ልባም እንድንሆን ነው ያስተማረን። የእየሱስ ተከታይ የሆነ ማንም ሰው የጌታን ፈቃድ የሚያስተውል የዋህ እንጂ እንጂ ሞኝ አይደለም።(1ቆሮ 2:16)

በእየሱስ የብጽዕና ትምህርት፣ የየዋሆች ተስፋ ምድርን መውረስ እንደሆነ ተመልክቷል። የመጀመርያው መውረስ በአሁኑ ጊዜ ባለን ህይወት የሚገለጥ ሲሆን ፣ሁለተኛው መውረስ ደግሞ ወደ ፊት በሚሆን ዘመን ነው። እንዴት ነው በየዋህነት ይህን ምድር የምንወርሰው ሳትሉ አትቀሩም። በብፅዕና ትምህርት እውነት፣ሰው ምድርን ሊወርስ የሚችለው ፣ያለውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሲሰጥ ነው። ያለው ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነ የሚቆጥር ሰው ደግሞ ፣ የእኔ የሚለው ነገር ስለማይኖረው የሚመካበት አንዳች ነገር እንዳለው አያስብም። ይህ ሰው፣በምድር እግዚአብሔር የሚወደውን አይነት ሕይወት የሚኖርና ከእርሱ ጋር ላለው ሰው የሚመች መሆኑ እርግጥ ነው። እንግዲህ የክርስትያናዊ ኑሮ መገለጫ “ እኔ በምድር ላይ ምን ያህል ተመችቶኝ ነው የምኖረው? ሳይሆን “እኔ ለሌላው ሰው ምን ያህል ምቾት እየሰጠሁ ነው? በሚለው ስሌት የሚለካ ነው። ምንም እንኳን ይህ ዓለም የአማኞችን ኑሮና አስተሳሰብ እንደ ሞኝነት ቢቆጥረውም፣ በኢየሱስ የተገለጠው የዋህነት ግን በእንዲህ ዓይነት መንገድ ምድርን የሚያስወርስ የአኗኗር ዘይቤ ነው::

ርግጥ ነው፣ማንም ሰው በጌታ ፊት ብፁዕ በሚያሰኝ የየዋህነት ስርዓት ሊመላለስ ከወደደ ፣በምድር የሚያጣቸው አያሌ ነገሮች እንዳሉ ሊያውቅ ይገባል። ሰው ሁሉ የተፈጠረበትንና በምድር የቆየበትን ዋና ነገር ሊፈጽም የሚችለው ግን ክርስቶስን በሕይወቱ መተረክ እስከቻለ ድረስ ነው። ስለዚህ ይህ ምስጥር ለገባው ሰው፣ምድርን የመውረስ መንገድ ያን ያህል ከብዶ አይታየውም። የገባው አሜን ይበል::

ይህ ጽሁፍ በጸጋ የመጽሔት አገልግሎት ለውይይት እና ለጥናት በሚመች መልኩ ከመጋቢ መርዓዊ ንጉሴ “ቱንቢ” ላይ የተወሰደ ነው:: ቱንቢን ሙሉውን ለመግዛት www.tsega.com ይጎብኙ